የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

News news
2026-03-13 10:57:15

   የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 3፣ 2018 (ወራዩ/ ህ /አ /አ /ግ) አለም አቀፉ የሴቶች ቀን (March "50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በወራቤ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተከብሯል።

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ተውፊቅ ጀማል የሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትን በማረጋገጥ ሂደት ባለፉት 50 ዓመታት የሴቶች ሚና ጎሎቶ የወጣበትና በተሰጣቸው ኃለፊነትም ስኬታማ መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጥ የቻሉ በርካታ ሴቶችን መኖራቸውን ያየንበት ነው ብለዋል።

ይህን አቅምና ጥረታቸውን ይበልጥ ማጎልበት የሚቻለው በዘርፉ የወጡ ህጎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፎዚያ አሚን ሴት ምሁራን እውቀታቸውን በመጠቀም ፍትህ የሰፈነበት ማህበረሰብ በመገንባት፣ በዕውቀት የበለፀገ ትውልድ በማፍራትና ሀገርን በማቃነት ሂደት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሴቶች ቀን (March -8) የሴቶች መብት የተከበረበት ብቻም ሳይሆን የዕውቀት ነፃነትም የተረጋገጠበት ነው ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት የማእከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቀመሪያ ረሻድ ባለፉት 50 ዓመታት ለሴቶች በተሰጠው ልዩ ትኩረት በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች የሴቶች የውሳኔ ሰጪነትና ተሳትፎ እያደገና እየተረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በበዓሉ የ50 አመት የለውጥ ጉዞና ማርች 8 በሚል በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ስራ አስጻሚ ወ/ሮ ሽቱና ሳዲቅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን ሚና በሚል በመምህርት ዘይቱና አማን ሰነዶች ቀርበው የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን የተለያዩ የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጽሁፍ ስራዎችም ቀርበዋል።

በመድረኩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የአለም የሴቶች ቀን በዓል ታዳሚያን የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ህጻናት ማቆያ፣ ዳታ ሴንተር እና ሌሎች የመሠረተልማት ስራዎችን እንዲሁም የወራቤ ከተማ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጎብኝተው የበዓሉ አከባበር መርኃ-ግብር ተጠናቋል።

                                                                                             

photo_2026-03-13_12-36-38-570100.jpg photo_2026-03-13_12-36-47-578930.jpg photo_2026-03-13_12-36-51-755930.jpg photo_2026-03-13_12-37-01-874442.jpg photo_2026-03-13_12-37-09-696503.jpg photo_2026-03-13_12-37-19-838212.jpg photo_2026-03-13_12-37-33-254167.jpg photo_2026-03-13_12-37-39-175225.jpg photo_2026-03-13_12-38-22-439204.jpg