ወራቤ ዩኒቨርሲቲ የ2019 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ

News news
2026-10-27 06:01:00

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ የ2019 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ

 

ጥቅምት 16/2019 (ወራ/ ዩ/ ህ/ አ /አ /ግ) ወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሪሜዲያል ፕሮግራምን ተከታትለው ያለፉ እና አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ እየተቀበለ ይገኛል። 

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር-ኢንጂነር ተውፊቅ ጀማል በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው፣ ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊና ለተማሪዎች የሚመች ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎች በቆይታቸው  በዕውቀት ፣ በምርምርና እንዲሁም በቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዲያበቁ በርትተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።  በሁሉም ዘርፍ ለተማሪዎች የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች ጥራታቸው ተጠብቆ  አስፈላጊው  ቅደመ ዝግጅት ተጠናቆ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን ገልፀው እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከተማሪዎች ጋር ያለው የልጅና የወላጅ ቤተሰባዊ መስተጋብር ለተማሪዎች ውጤታማነት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከአዲስ ገቢ ተማሪዎች ጋር ከከተማው ማህበረሰብ ጋር የአማና/ ቃል ኪዳን ትስስር የመፍጠር ስራ እንደሚሰራ ገልጸው መልካም የትምህርት ዘመን ተመኝተዋል።

 

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳዲቅ አህመዲን ወደ ወራቤ ከተማ እና ወደ ዩኒቨርሲቲው በ2019 ዓ.ም ተመድበው የመጡ  ተማሪዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። ወራቤ ከተማ የሰላም ሰገነት፣ የአብሮነትና የፍቅር ከተማ መሆኑን ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩ ተማሪዎች ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት ቤተሰባዊ በማድረግ ከተማው እንደቤታቸው እንዲሰማቸው የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል። ተማሪዎች ዛሬ የጀመሩት አዲሱ የህይወት ምዕራፋቸው ለቀጣይ የህይወት አቅጣቸው ስንቅ በመሆኑ በርትተው እንዲማሩ ጥሪ አቅርበው፣ መልካም የትምህርት ዘመን ተመኝተዋል። የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጎህ የባህል ቡድን አባላት በተማሪዎች አቀባበል መርኃግብሩ ላይ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች  አቅርበዋል።

በአቀባበል መርኃግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላት፣ የሀይማኖት አባቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

 

ዕውቀት ለልህቀት

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ

 


1000050542-910865.jpg 1000050544-557596.jpg 1000050543-567292.jpg 1000050545-196380.jpg 1000050541-946767.jpg